WAO- We All One! Ethiopians!

WAO- We All One! Ethiopians!

Monday, May 4, 2015

የአሜሪካ የውጪ ፖሊሲ የድንቁርና መግለጫ ወይንስ የፅንፈኝነት እብሪት::

                                                ሚያዝያ 13/2007 April 21/2015                                                             አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለምዕራባውያን ያለን አመለካከት በእጅጉ እየተለወጠ የመጣው በወያኔ ዘመን ነው:: ምዕራባውያን ብለን የምንጠራቸው አገሮች ከመርህ ተነስተው በዲሞክራሲ የሚሰጡት ስፍራ አለ ብሎ በማጋነን ያየው የነበረው እይታው የተለወጠው የትግሬ/ወያኔ አገዛዝ ስልጣን ላይ ቁጢጥ ካለበት ጊዜ ወዲህ ነው:: ምንም እንኳን የቀዘቃዛው ጦርነት ተብሎ ይጠራ በነበረበት ዘመን በጥቂቱ ከ30 ዓመቶች በፊት ምዕራባውያን ሰው በላ የሆኑ መሪዎችን አቅፈውና፣ ደግፈው፣ አሞካሽተው እሽሩሩ ይሏቸው እንደነበር የቅርብ ትዝታ ቢሆንም፣ እንደአሁኑ ዘመን በተለይም አሜሪካ አለም አቀፋዊ እይታዋ ይህን በመሰለ ሁኔታ ይለወጣል የሚል ግምት በማንኛችንም ግምት ውስጥ አልነበረም:: ከሶቭየት ሕብረት መውደቅ በፊት በፀረ ኰሚኒዚም አባዜ የተተበተበው ፖሊሲ ወደ ፀረ ሽብርተኝነት ምትሃታዊ ቅዠት ከተለወጠ ወዲህ ዓለምን የሚጋልበው አንድና ብቸኛ ሃያል ሆኗል:: የአሜሪካ የውጪ ፖሊሲ ከአገሮች ጋር ቅራኔ ገብቷል:: የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ከሕዝብ መብትና ጥቅም፣ ከአገር ሕልውና በላይ ሆኗል:: በምዕራባውያን አገሮች መካከል በተለይም በአፍሪካ የመልካም አስተዳደር እና የዲሞክራሲያዊ ስርአት መስፋፋትን ትኩረት ሰጥተንበታል በሚል ሽፋን በሎሌ መሪዎች አማካይነት በመፈፀም ላይ ያሉ ደባዎች የአገራችንን ችግር ውስብስብ በሆኑ ሰንሰለቶች እያቆላለፉት መጥተዋል:: የአሜሪካ ወታደራዊ ጀብደኝነት ያስከተለው መዘዝ አላማችንን ወደ አልተረጋጋ ሁኔታ ወስዷታል:: በአሜሪካ በኩል ሃይልን ጨምሮ የመራመድ ፅንፈኛ አቅጣጫ አለምን በምስሏ ለመቀረፅ ከምታደርገው ምኞቷ ጋር የተያያዘ ነው:: ይህ ፅንፈኛና ብቸኛ ልዕለ ሃያል ሆኖ መገኘት ያስከተለው ጀብደኝነት ሰብአዊ ፍጥረት ለሆነው ሁሉ የሕሊና ቁስል እየሆነ መጥቷል:: ከቀድሞዋ ከሶቭየት ሕብረት መፍረስ በፊት አሜሪካኖች በነበራቸው የፀረ ኰሚዩኒዝም ትግል ሳቢያ፣ ከትቢያ ያነሷቸውን የፀረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ወያኔና ሻቢያን አቀላምጠው በመያዝ ለሥልጣን ካበቋቸው ወዲህ በኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና ላይ ደባ እየተፈፀመባት ይገኛል:: አለአሜሪካኖች ድጋፍ እንደማይኖር የተረዳው ወያኔ የታዘዘውን በመፈፀም ተላላኪ መሆኑን በማረጋገጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በህይወቱ ዋጋ እየከፈለበት ነው:: ምዕራባውያን ይህን የዘመናችንን ሎሌና ተላላኪ አገዛዝ በመዳፋቸው ውስጥ የገባ እያለ ሌላ አማራጭ ያስባሉ ወይንም በዲሞክራሲ መስፈርት ይመራሉ ብሎ ለመገመት የማይቻልበት ወቅት ተደርሷል:: ከአክራሪ ኰሚንስትነት ከመቀፅፈት ወደሎሌነትና የነሬገንን ኒኦ-ኰንሰርቫቲዝም አክራሪ ፖሊሲ ቡራኬ የተቀበለው የአንድ የዘር ቡድን ስልጣን ከመያዙ በፊት ጀምሮ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ጋዜጠኞ፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ፖለቲከኞችን በወዳጆቻቸውና በሎቢ (Lobby) ኩባንያዎች በኩል ያጠናቀቁት ሽርክና ስለነበር ዛሬ በመንግሥት ስልጣን ባለቤትነቱ በእጁ ያስገባው ሃብት ለድለላ እና ለሽንገላ እንዳሻው ለመጠቀም ሁኔታው በመፍቀዱ የተቃዋሚ ድርጅቶች ድምፅ ባዶ ሜዳ ላይ እየወደቀ መጥቷል:: 2 እኛ ኢትዮጵያኖች ምዕራባውያን በተቀዳሚ አሜሪካኖች በኢትዮጵያ የሚደረገው የዲሞክራሲ ትግል በፍትሐዊነት የሚጠናቀቁበት ሁኔታ ይደግፉ ይሆናል ብለን ማሰብ ሳይሆን፣ በምን ዓይነት የመራራ ትግል ወደፈለግነው ግብ ለመድረስ በሚከፈለው መስዋዕትነት ዙሪያ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ግንዛቤዎችን ካገኘን ብዙ ዓመቶችን አስቆጥረናል:: የወያኔ ወዳጆችና አሽቃባጮቻቸው ለፍትሃዊ ፍለጋ የሚደረገውን መራራ ትግል እንዲታያቸው፣ በመጪው ዘመን የተበደለ ሕዝብ የምስራች የሚበሰርበት መሆኑን ለማስገንዘብ እየዳህን ካለንበት የትግል ጉዞ መነሳት ይኖርብናል:: ፍትሃዊ አማራጭ በልመና አይመጣም፣ አሜሪካኖች ጋዜጣዊ መግለጫ አይሻርም፣ ፍትሃዊ ጥቅማችንን በእጃችን ውስጥ የምናስገባው ወያኔን የሚደግፉትን ስትራቴጅካዊ ጥቅማቸው ጋር ስንጋጭ ነው:: ይህን ሲያዩ ለመፍትሔ ፍለጋ፣ ለድርድር ይጣደፋሉ:: አሜሪካኖች የሚደግፉት አገዛዝ ቁመናው አሳፋሪ፣ ባህሪውም ጋጠ ወጥ፣ ዘረኛ አገዛዝ መሆኑን ያውቁታል:: ለውጪ መንግሥታት አቤቱታ የሚያቀርብ፣ ማመልከቻ ይዞ የሚንከራተት፣በአውሮፓ መንገዶች የሰላማዊ ሰልፍ ጩኀት ብቻውን ምዕራባውያን ከስትራቴጂካዊ ጥቅሞቻቸው አንፃር የያዙትን መሞዳሞድ አንዳችም ስንዝር ፈቀቅ አያደርጋቸውም:: ከዚህ በላይ መጠናቀቅ ያለባቸው ጉዳዬዎች እንዳሉ ኢትዮጵያዊነት ጠንቀቆ ያውቃል:: በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ብሎም ችግሮችን ለማስወገድ ክብራችንንና ነፃነታችንን ለማስከበር ለምንወስደው እርምጃ የማንንም መንግሥታት እውቅና አንጠብቅም:: በትግሬ/ወያኔ አገዛዝ መዘዝ ምክንያት ሉዓላዊነቷ ከተተበተበበት ችግር በማላቀቅ ለሕልውናችን የሚያስፈልገውን ሰላምና ብልፅግና ለዚህ ደግሞ በመሣሪያነት እጅግ ፍቱን የሆነው የዲሞክራሲ፣ የመብትና የሕግ የበላይነትን ጥያቄ በአስተማማኝ ሁኔታ በአገራችን የሚዘረጋበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሐላፊነቱን በዜጐቿ እጅ ላይ የወደቀ ነው:: ላለፉት 24 ዓመታት በአገራችን ኢትዮጵያ አገዛዙ በስልጣን ላይ ለመቆየትና የአገዛዙን በዘር ሐረግ የተዋቀረ የስልጣን ሽግግር ዘለዓለማዊ ለማድረግ ሲል በሚፈፅማቸው ከስብዕና የራቁ ተግባራትና የበቀል ወንጀሎች የተነሳ እጁ በንፁሐን ደም የጨቀየ ነው:: አገራችን በቀማኞች፣ በነፍሰ ገዳዬች፣ በነፃነት ጠላቶች፣ ዜጐችን በፍርሃት ሸብቦ፣ ሰብአዊ ክብርና አዋርዶ በችግርና በመከራ ቆፍድዶና አስጨንቆ ለዘለ ዓለም ለመግዛት ግጭቶችን በሚያቀጣጥል መከራ ተሰንጋ ተይዛለች:: ሕግና ሕግጋት መኖሩን ለመናገር የሚያስችል ተጠየቅ ስለሌለ አገዛዙ በጥይት ይገድላል፣ ቀጥቅጦ ይገድላል፣ አስሮና አሰቃይቶ ይገድላል፣ የዜጐችን ቤት ያፈርሳል፣ የአርሶ አደሩን መሬት ነጥቆ ይሸጣል፣ ሕዝብን ያፈላቅላል ሕግና ሕጋዊነት ሽታውም የለም ለአገዛዙ ሕግ ማለት ሐይል ነው:: አገዛዙ ለራሱ ዘር ብቻ ካልሆነ ለቀረው ደንታ የለውም:: የኢትዮጵያውያኖችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በቅርብ ሲከታተል የነበረው የአሜሪካ መንግሥት ከሰሞኑ ድንቁርናና ዕብደት በተቀላቀለበት መልክ ለወያኔ አገዛዝ ምስክርነቷን ሰጥታለች:: መግለጫውን አስመልክቶ የተለያዩ ትችቶች ሲሰነዘር ሰንብቷል:: የተቃዋሚው ወገን በወጉ የተሰላ የትግል አካሄድና ድርጅታዊ አቅሙም አመርቂ ደረጃ ላይ አለመገኝት ያስከተለው ሁኔታ የወያኔ ጌቶች ንቃታቸውን እያሳዩ መጥተዋል:: ይህ ንቀት አሜሪካኖች ብሔራዊ ጥቅማችን ብለው ከያዙት መርሆ ጋር የተያያዘ ነው:: በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን የዲሞክራሲ ሻምፕዬን የምትባለው አሜሪካ በጉልበታም ስርአት የጭካኔ መዳፍ ውስጥ ገብተን በአንድ ዘር ወደአስከፊ ቀውስ እየተጓዝን መሆናችንን አያዩትም ለማለት አያስደፍርም:: ሚሊዮኖችን ረግጦ እየጨፈለቀ፣ አስሮ እያንገላታ ከሃገር እያሰደደና እየገደለ ለ25 ዓመታት መቆየቱን አላጡትም:: የሰሞኑን የድጋፍ ንግግር አደረገች የተባለችዋ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር፣ ምክትል ሚኒስተር ዌንዲ ሸርመን ከሱዛን ራይዝ በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት በአምባሳደር ደረጃ የአሜሪካ ተወካይ 3 ጋር በ80ኛዎቹ በሱዳን ተቀማጭነታቸውን አድርገው በጋዜጠኝነት እና በአሜሪካ የሰለላ ድርጅ (CIA ) ሲሰሩ ከፀረ ኢትዮጵያ ሐይሎች ጋር ማለትም ከወያኔና ሻቢአ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸው የዘመኑ ሹማምንቶች ናቸው:: እነዚህ ሁለት ሴቶች የአሜሪካ አስተዳደር ባለስልጣናት ለወያኔና ለሻቢአ ብዙ ውለታ የዋሉ ናቸው:: ሱዛን ራይስና ዊንዲ ሸርመን በ80ዎቹ በሱዳን እየተንሸራሸሩ የኢትዮጵያን አንድነት ከሚያጠፋ ሃይሎች ጋር በመሆን ሲያሻቸው ከሱዳን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ሕወሐት የኰሚኒስትነት ካባውን ጥሎ አሜሪካ አድርግ የሚለውን ቢፈፀም ሥልጣኑ ወደእነሱ ሲተላለፍ እንደሚችል ያማለዱ ናቸው:: እንቀደሙት ጊዜያት ሁሉ የአሜሪካ የፅንፈኛነት የቀኝ አክራሪ ፖሊሲ የአገሮችን መብት ሲጋፋ የቆየ ነው:: በተለይም አሜሪካ ብቸኛዋ ልእለ ሃያል መንግሥት በመሆኗ በአለማችን ያላትን ተፅእኖ የምትገልፅበት መንገድ በንቀት ላይ ያረፈ ነው:: ዓላማዋን ያልተከተለ በወታደራዊ ጉልበቷ ታዳሽቃለች:: ወታደራዊ ቁመናዋ ማንም ሊጋፈጠው እንደማይችል ሙሉ ዕምነት ቢኖራትም በየአገሩ የደረሰባት መቀጣትና ውርደት ግን የሚናቅ አይደለም:: ዛሬ በየጊዜው ከዲክታተሮች ጋር በመሞዳሞድ ዓለምን ለመጋለብ የምታደርገው ሙከራ አላማችንን ወደ አልተረጋጋና የጥፋት ዘመን እያደረሰችን ነው:: አሜሪካኖች ወያኔን ዲሞክራቲክ መንግሥት ነው በሚል ሰርትፍኬት ሰጥተው አሸናፊ አድርገው የማውጣት ፍላጐታቸው የተያያዘው ወያኔን እንዳሻቸው ሊጋልቡት ስለሚችሉ ነው:: በሱማሊያ፣ በሱዳን፣ በምዕራብ አፍሪካ የተጫሩ እሳቶች ለማብረድ በምዕራባዊያን ትዕዛዝ ባምሳያው የፈጠረውን የጦርና የፀጥታ ሃይል በሕዝብ ለማዝመት ሳንጃውን ስሎ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ነው:: የአገሩን ዜጋ እየገደለ፣ እያፈነ፣ እያፈናቀለ በመከራና በስቃይ እያኖረ የተጫረ እሳት ለማጥፋት በዶላር ስጦታ ወዶዘማች የሚመለምለው ወያኔ ነው:: አሜሪካኖች በአህጉሩ እየተከሰተ ያለውን የቅራኔዎች መስፋፋት በማስቀጠል የስርዕት መናጋት በሚፈጠረው ሁኔታ ብሔራዊ ትቅማችን ያሉትን ለማስከበር የመረጡት የትግሬ/ወያኔን አገዛዝ ነው:: አሜሪካኖች ወያኔን አፍቅረንሃል ስላሉት የእልቂቱ ቀጠና አድርጐ የያዘው የከፋፍለህ ግዛ ቅራኔ ይባባሳል እንጂ አይበርድም:: በዚህ አቋማቸው እስከቀጠሉ ድረስ የዘለቄታ ብሔራዊ ጥቅም ያሉትን በወያኔ በኩል ለማስጠበቅ እንደማያስቸግራቸው መታወቅ ይኖርበታል:: የወያኔ እመቃ ዘለዓላማዊ አይደለም:: ሁላችንም እንደምናውቀው አሜሪካና እንግሊዝ በኬንያ አለሕዝብ ፈቃድ እያጭበረበረ በስልጣን ላይ ይቀመጥ የነበረው የአራፕ ሞይ አገዛዝ አቅፈውና ደግፈው ካቆዩት በኋላ በአመፅና በእንቢተኝነት ሊወገድ ችሏል:: የምዕራብ አገሮች ሕዝባዊ ቁጣ እስኪያዩ ድረስ በከፍተኛ የቅንጦት ደረጃ የተንደላቀቀ ህይወት እንዲኖሩ የሞራል የሚሊተሪና የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት አጉራ ዘለል አገዛዞች ዜጐቻቸውን ቀጥቅጠው እንዲገዙ ይፈቅዳሉ:: ዛሬ በአረቡ ዓለም የፈረሱትና ያሉት አገዛዞች የዚሁ የምዕራባውያን የብሔራዊ ጥቅም ውጤቶች ናቸው:: ምዕራባውያን መልካም አስተዳደር ግልፅነት እና ተጠያቂነት ያለው መንግሥት ይምጣ የሚሉት በሕዝባዊ ማእበል እንቅስቃሴ ሲተገበር ብቻ ነው:: የአገዛዙ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር የታጠቀ ሃይል ቢሰለፍ፣ እልፍ አእላፍ ፌርማቶሪዎች በሕዝብ መካከል ቢሰገሰጉ፣ ሚሊዮኖዎች ካድሬዎች ሃገር ምድሩን ቢያጥለቀልቁት የዘረኛው የትግሬ/ወያኔ አገዛዝ የፖለቲካ ክስረት እስካለ ድረስ ወሳኙ ጊዜ ነው:: የትኛውም ምድራዊ ሃይል ሊያመክነው የማይችል አብዬት መቀጣጠሉ አይቀሬ ነው:: ይህን ከታሪክ ማስታወሻ ጋር አያይዘን እንግለፅ:: የነጀነራል መንግሥቱ ነዋይ የታህሣሡ ግርግር እየተባለ በሚጠራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ ተከተሎ ጄኔራሉ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ 4 ዋ! ዋ! ዋ! ለእናንተም፣ (ለዳኞቹ ማለት ነው) ለገዢዎቻችሁ ጨመሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት የሚነሳበት ጊዜ የሚደርስባችሁ መዓት የሚያሰቅቅ ይሆናል በሚል ተናግረው ለስቅላት በቅተዋል:: ያ ትንቢት ከ13 ዓመቶች በኋላ ከእጥፍ በላይ መፈፀሙን ስናስታውስ በጥቅመኝነት ስሌት ከስርዓቱ ጋር ተወዳጅተው የግፉአንን የመከራ ዕድሜ የሚያራዝሙ ሆድ አደሮችም ሆኑ የአገዛዙ ህሊቃን፣ ሕዝብ ””ሆ ”” ብሎ በአንድነት የተነሳ ዕለት ዶጋ አመድ መሆናቸው አይቀሬ ነው:: ለነገሩ ይዘግይ እንጅ ታሪክ በእውነት እንጅ ከፍረሃት ጋር ውል ኖሯት አያውቅም:: በዘውግ ማንነት ማለፍ ግድ የሆነባት አገር፣ የወፍን ያህል የራስ ጐጆ መመኘት እንኳን እንደ ህብሰተ መና በራቀበት ምድር፣ ዜጐች በምርኰኛ ሕግ ተቀፍድደው ውለው በሚያድሩበት ክልል፣ መማር ድንጋይ ከመፍለጥ በማያሸጋገርበት ዘመን የመኖርና ያለመኖር ግድግዳው ጣራው ተደርምሶ ሁሉም ነገር ከንቱ በሆነበት አገር ዝምታው መጥፊያችን ሆኗል:: አጋሮቻቸውም ሞትን በይነውብናል :: ስለሆነም ትግላችን የአሜሪካንን ላይሰንስ አይጠይቅም:: ጭቆና፣ በደል፣ ግፍ አለብን ካልን፣ የማሸነፊያ ብቸኛ መንገድ የፍርሃትን ሰንሰለት ሰባብሮ በዘረኞች ፍቃድ ለቆመው ስርአትም ሆነ በድምፅ አልባ ተወካይዎች አጃቢነት ለፀደቁት ሕግጋት አለመታዘዝን በፊት ለፊት ስናስተጋባ ብቻ ነው:: በእምቢተኝነት ደም አልባ ሰላማዊ አመፅ የገዥዎችን ሰፈር ስናርበደብድ ብቻ ነው:: አደባባይዎችን በሰው ጐርፍ ማጥለቅለቅ ስንችል ብቻ ነው:: ለመብታችን፣ ለነፃነታችን፣ ለክብራችን እስኪንበረከኩ ድረስ በትግል በፅናት በመቆም ቁርጠኝነታችንን ስናሳይ ነው:: የትውልድና የአገር ደዌዎችን የምንገላገለው ሰፊና ቆራጥ ሕዝባዊ ሃይል ወደ አደባባይ ስናወጣ ብቻ ነው:: ይህ ሲሆን ብቻ ነው የወያኔ ሸሪኰች እጃቸውን የሚሰበስቡት::                                                                                                                                                                      ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ! ከስቶክሆልም ስዊድን

No comments:

Post a Comment

Note: Only a member of this blog may post a comment.